ራዕይ

በ2012 ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝ፣ ምቹ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ አቅምን ያገናዘበ የብዙሀንና የጭነት ትራንስፖርት ለህብረተሰቡ ማቅረብ፡፡

ተልዕኮ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለስልጣን በህዝብና በጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ ማህበራትን፣ ተቋማትንና ግለሰቦችን በማደራጀት፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማልማትና በማስተዳደር፣ ጥናቶችን በማካሄድ፣ ስምሪት በመስጠት፣ በመቆጣጠር እና መረጃን ተደራሽ በማድረግ ተገልጋዩ ህብረተሰብ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፡፡

እሴቶች

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዕሴቶች በሁሉም አመራሮችና ፈጻሚዎች እንደ መመሪያ በእለት ተእለት ሥራ ውስጥ በአመራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ወቅት ልንከተላቸውና ልንላበሳቸው የሚገቡ ወሳኝ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ በተቋሙ የተመረጡ እሴቶች፡-

    ተጠያቂነት
ግልፅነት
          የላቀ አገልግሎት
            ለለውጥ ዝግጁነት
  ፍትሀዊነት

ስልጣንና ተግባር


ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሆኖ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1) በከተማው ትራንስፖርትን በተመለከተ ተገቢውን መረጃ ያደራጃል፣ ያሰራጫል፡፡  

2) የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት ፕላንና ፕሮግራም ከከተማው የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ጋር አጣጥሞ ያዘጋጃል፤ ሲፈቀድለትም ተግባራዊ ያደርጋል፤

3) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በትራንስፖርት ዘርፍ የሚሠሩ ማኅበራት እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ ተገቢውን ድጋፍ ይሰጣል፤ ማኅበራቱ ለከተማው ትራንስፖርት  ቅልጥፍናና ደህንንት መሥራታቸውን ያረጋግጣል፤

4) በከተማው አስተዳደር ለተሸከርካሪዎች አገልግሎት የሚውሉ መናኽሪያዎችንና ፌርማታዎችን ይገነባል፣ መጋዘኖችና ዴፖዎችንም ያስተዳድራል፤

5) የከተማውን የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ይገነባል፣ ያስፋፋል፣ ይጠግናል፣ ያስተዳደራል፤ 

6) የተቀናጀ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት ሥርዓት ያደራጃል፣ እንዲስፋፋም ያደርጋል፤

7) የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ አሽከርካሪዎችና መሰረተ ልማት መመሪያ፣ ስታንዳርድና ስፔስፊኬሽን ማዘጋጀት፣ ተግባራዊነቱን          ይቆጣጠራል፣

8) የከተማውን የትራንስፖርት ታሪፍ ያወጣል፣ የከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት በቅንጅት እንዲሰሩ ዕቅድ ያወጣል፤ 

9) ትራንስፖርቱን የሚመለከቱ የፖሊሲ ሃሳቦችን አዘጋጅቶ ለቢሮው እና ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፣ ሲፈቀድለትም ተግባራዊ ያደርጋል፣

10) የመንግስት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን በበላይነት ይመራል ይቆጣጠራል፣

11) የህዝብና የጭነት ትራንስፖርትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ ፈጣን ተደራሽና ፍትሃዊ እንዲሆን ያደርጋል፣

12) የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዱ ጥናቶች ያካሂዳል፣

13) የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት ሰጪ ማህበራትና ተቋማትን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል፣

14) የህዝብ ትራንስፖርትን አገልግሎት የተቀናጀ የክፍያ ስርዓት በመዘርጋት ተግባራዊነቱን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣

15) የከተማውን የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት የሥምሪት ጊዜ ሰሌዳ ያወጣል፣

16) ለሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ ይሰበስባል፣

17) የንብረት ባለቤት ይሆናል በስሙ ይከሳል ይከሰሳል፣

18) ዓላማውን ለማስፈጸም ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፣